በባህሬን ንጉሳዊ መንግስት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት አዘጋጅነት ‘’ጳጉሜ 1 ቀን 2016 ዓ.ም የመሻገር ቀን እና የ2017 አዲስ አመት” በደማቅ ሁኔታ ተከበረ።
***********************************************************
በመሻገር ቀን አከባበር ላይ በባህሬን የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዉያን፣ ትዉልደ ኢትዮጵያዉያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተገኝተዋል። የዝግጅት መርሃ ግብሩ በሃይማኖት አባቶች ጸሎተ ቡራኬ የተከፈተ ሲሆን አሮጌውን ዓመት ስንሸኝ በመጪው አዲስ ዓመት ለሀገራችን የሠላም፣ የፍቅር፣ የእርቅና የትብብር ጊዜ እንዲሆን እንዲሁም ራሳችን የሠላም ተምሳሌት በመሆን አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ መቀበል እንደሚገባ መልዕክት ተላልፏል።
በዚሁ በመሻገር ቀን አከባበር ላይ በባህሬን ንጉሳዊ መንግስት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቆንስል ጄኔራል ክቡር አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ፣ 2016 አገራችን በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ በመሆን ከፍተኛ ዘመን ተሻጋሪ ልማቶች በመስራት ለዜጎች የስራ ዕድልና ለነዋሪዎቿ ምቹ አከባቢ መፍጠር የተቻለና የነበረውን የውስጥና የውጭ እንቅፋቶች የተሻገረችበት መሆኑን በመግለጽ፣ አዲሱ አመት በተሰማራንበት የስራ መስክ የተሻለ ውጤት በማምጣት፣ አቅም የሌላቸው እህት ወንድሞቻችንን በማገዝና በአቅማችን የአገራችንን ልማት የምንደግፍበት ሊሆን እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ክቡር አምባሳደር በመቀጠልም በመንግስት እየተከናወኑ ከሚገኙ ታላላቅ ፕሮጀክቶች መካከል የተላቁን ህዳሴ ግድብ ፣ሃላላ ኬላ፣ የጎርጎራና የወንጪ ደንዲ ፕሮጀክቶች እንዲሁም አዲስ አበባን ለማስዋብ የተካሄዱ የተለያዩ የኮሪደር ልማቶችን በማስታወስ ለነዚህ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ ለማፈላለግ በቆንስላ ጄኔራል ፅ/ቤታችን በኩል በተካሄዱ የገቢ ማስባሰቢያ ፕሮግራሞች ላይ በመሳተፍ የእራሳቸውን አሻራ ላኖሩ በባህሬን የዲያስፖራ ማህበረሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማትና ለንግዱ ማህበረሰብ ምስጋና በማቀርብ በቀጣይ ለህዳሴው ግድብ የመጨረሻ ዙር የገቢ ማሰባሰብ ላይ ከሚሲዮኑ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ክቡር አምባሳደር ለመቀበል በተዘጋጀነው 2017 አዲስ አመት ተስፋ የምንሰንቀበት ፣ አዳዲስ ውጥኖችን ለማሳካት የምንተጋበት ፣ የለውጥ እና የስኬት ዓመት እንዲሆን ምኞታቸውን የገለፁ ሲሆን በዝግጅቱ መርሃ ግብሩም የጋራ አንድነትን በሚያጎለብቱ የተለያዩ ፕሮግራሞች ታጅቦ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook